የፕሬስ መግለጫ
ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት 1,576,271 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለገበያ አቀረበ
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2016 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ገበያ ብር 9,873,711,801 ዋጋ ያለው 1,916,676 ኩንታል መሠረታዊ ምርትና አገልግሎት ለማሰራጨት አቅዶ ብር 9,410,363,580 ዋጋ ያለው 1,576,258 ኩንታል ምርትና አገልግሎት በማሰራጨት ዕቅዱን በመጠን 82 በመቶ በዋጋ ደግሞ 95 በመቶ አከናውኗል፡፡
በሀገር ውስጥ ገበያ ኮርፖሬሽኑ ብር 7,939,329,584 ዋጋ ያለው 1,493,676 ኩንታል ምርትና እና የአገልግሎት ሽያጭ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ አቅዶ ብር 6,577,795,218 ዋጋ ያለው 1,108,610 ኩንታል ምርት እና የአገልግሎት ስርጭት በማከናወን የዕቅዱን በመጠን 74 በዋጋ ደግሞ 83 በመቶ አከናውኗል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት በውጭ ገበያ 423,000 ኩንታል እህልና ቡና በብር 1,934,382,217 ለመሸጥ አቅዶ 467,648 ኩንታል ስንዴ፣ ሰሊጥ እና ቡና በብር 2,832,568,362 (50,590,069 የአሜሪካ ዶላር) በመሸጥ የዕቅዱን በመጠን 111 በመቶ በዋጋ ደግሞ 146 በመቶ አከናውኗል፡፡
የግዥ አፈጻጸምን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ በአጠቃላይ ሊገዛው ያቀደው መሠረታዊ የምርት አቅርቦት መጠን ብር 9,089,404,311 ዋጋ ያለው 1,978,007 ኩንታል ሲሆን በዚህ ወቅት ብር 10,861,975,414 ዋጋ ያለው 2,060,413 ኩንታል በመግዛት የዕቅዱን በመጠን 104 በመቶ በዋጋ ደግሞ 120 በመቶ አከናውኗል፡፡
ለአምራቹ ምርት ገበያ በመፍጠር የተከናወኑ ተግባራት፡-
ከኮርፖሬሽኑ ቁልፍ ተግባራት አንዱ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በቀጣይነት መደገፍና ለምርቱ አስተማማኝ ገበያ መፍጠር ሲሆን በበጀት ዓመቱ 1,558,095 ኩንታል እህልና 3,425 ኩንታል ቡና እንዲሁም 69,953 ኩንታል ፍራፍሬ እና አትክልት ከምርት አቅራቢዎች ግዥ አከናውኗል፡፡
በሌላም በኩል የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ያመረቱትን ምርት ተቀብሎ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሰራጨት በዓመቱ 310,259 ኩንታል ምርት በመግዛት ለአምራቹ የገበያ ዕድል ፈጥሯል፡፡
የአቅርቦት እጥረትንና የዋጋ ንረት ለመከላከል የተደረገ ጥረት፡-
ኮርፖሬሽኑ የምርት አቅርቦት እጥረትንና የዋጋ ንረትን በመቀነስ ገበያውን ለማረጋጋት ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለማረሚያ ቤቶችና ለሌሎች ሸማች የህብረተሰብ ክፍሎች ብር 198,396,121 ዋጋ ያለው 23,743 ኩንታል ጤፍ፤ ብር 399,225,136 ዋጋ ያለው 63,927 ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ፤ ብር 1,370,238,100 ዋጋ ያለው 14,081,100 ሊትር የምግብ ዘይት፤ ብር 342,457,335 ዋጋ ያለው 50,050 ኩንታል ስኳር እና ብር 765,757,752 ዋጋ ያለው 100,616 ኩንታል ልዩ ልዩ የፍጆታ ሸቀጦች በማሰራጨት የተጠቃሚውን ህብረተሰብ የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት ጥረት አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል ለሀገር መከላከያ ቀልብ የሚሆን 310,659 ኩንታል ስንዴ እና 86,000 ኩንታል የስንዴ ዱቄት በማቅረብ ሀገራዊ ተልዕኮን ለመወጣት ጥረት ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም የምርት አቅርቦት እጥረትን ለመሸፈን በተለይም ለአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና ለዓለም ምግብ ድርጅት ብር 467,117,882 ዋጋ ያለው 123,800 ኩንታል በቆሎ ተሠራጭቷል፡፡
በግንባታው ዘርፍ የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረትንና ዋጋ ንረትን ለመከላከል ከፋብሪካዎች 120,323,924 ዋጋ ያለው 118,302 ኩንታል በቀጥታ በመረከብ ለተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ ማሠራጨት ችሏል፡፡
የሸማቹን ገበያ የማረጋጋት አሰተዋፅዖ በገንዘብ ሲመዘን፡-
ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አምራቹ ላመረተው ምርት ገበያ ከመፍጠር ባሻገር ከፍጆታ ሸቀጦች ጋር ያለዉን የዋጋ መወደድ በተለይም በልዩ ልዩ ሀይማኖታዊ በዓላት ወቅት በርካታ የፍጆታና ሌሎች ሸቀጦች ግዥ ሸማቹ ማህበረሰብ በስፋት የሚያከናውንበት ሁኔታ በመኖሩና ለዚህም ዝግጅት በማድረግ ገበያዉን ለማረጋገት የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በዚህ መሠረት 23,742 ኩንታል ጤፍ፣ 14,081,100 ሊትር የምግብ ዘይት፣ 49,894 ኩንታል ስኳር፣ 13,160 ኩንታል ሩዝ፣ 360 ኩንታል ቀይ ሽንኩርት እና ሌሎችም ምርቶች ከገበያው ዋጋ በጠቅላላ ብር 1,864,990,796 ቅናሽ በማድረግ ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት ተደርጓል፡፡
--//--